ቤተ ክርስቲያን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ የመሠረታት ሰማያዊ ተቋም ናት፡፡ በእርስዋም ጻድቃን (እውነተኞች) ይመላለሱባታል፡፡ ወደ እርስዋም የገቡ ከበደላቸው ነጽተው ጽድቅን ይለብሳሉ፡፡ ጻድቃን
ቡሩካንን በውስጧ ይዛለችና ቤተክርስቲያን በምድር የምትገኝ የእግዚአብሔር መንግሥት ምሳሌ ናት፡፡ የክርስቶስ ወንጌለ መንግስት የሚነገርባት፣ ለሰው ልጆች ኃጢአት ለማስተስረይ የሚፈተተው የክርስቶስ ሥጋና የሚቀዳው
ደም ለምእመናን የሚቀርብባት ምስጢራት የሚፈጸምባት የእግዚአብሔር ደጅ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንገባ የቅድስናን ሸማ እንለብሳለን፡፡
በሰማይና በምድር የሚገኝ ሁሉ የሚታየውና የማይታየው ግዙፉና ረቂቁ ሁሉ የእርሱ የሆኑለት እግዚአብሔር የሚከበርበት ቤተ መቅደስ በእኛ በክርስቲያኖች ዘንድ ልዩ እና ገናና ክብር ያለው ስፍራ ነው፡፡
ለአምልኮተ እግዚአብሔር የተለዩ ስፍራዎች በክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ ልዩ ክብር አላቸው። የቤተክርስቲያን ባለቤት ክርስቶስ ካለው ልዩ ክብር አንጻር ታላቅ ክብር ለቤተ ክርስቲያን እንሰጣታለን። በአንድነት እና ፍጹም በሆነ ክርስቲያናዊ ሕብረት እግዚአብሔርን የምናገለግልባት ለሰማዩ መንግስት ዝግጅት የምናደርግባት ይህች ልዩ ስፍራ ለአገልግሎት ምቹ በሆነ መልኩ መሰራቷ ለአማንያን ፍጹም ደስታ ነው፡፡
የይርጋ ዓለም (ጋኔ) ደብረ ታቦር ቅድስት አርሴማ ወደብረ ቁስቋም ቅድስት ማርያም አብያተ ክርስቲያናት ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የገጠር አብያተ ክርስቲያናትን በመደገፍ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን በመንፈሳዊ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን በሁለንተናዊ ልማት መስክም ጭምር ከፍ ብላ እንድትታይ በማደረግ ላይ የሚገኘው መልካም ሥራ ጎልቶ የሚጠቀስ ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የደብረ ቁስቋም ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውብ በሆነ ሁኔታ ተሰርቶ ተጠናቆ ለአገልግሎት በመብቃቱ ለአድባራቱ ምእመናን እንዲሁም ለመላው ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ታላቅ ደስታ ነው፡፡
አብያተ ክርስቲያናቱ ሕሙማነ ሥጋ፤ ፈውሰ ሥጋ የሚጎናጸፉበት፣ ያዘኑ የሚጽናኑበት፤
በመከራ ውስጥ ያሉ ፍጹም እረፍትን የሚያገኙበት በመሆኑ የካህናትና ምእመናን ደስታ የላቀ ነው፡፡
በዚህ ታላቅ ሥራ በአድባራቱ አስተዳዳሪ መልአከ ሕይወት ቀሲስ እንደሻው አብርሃ መሪነት በሕንጻ ኮሚቴነትና በተለያዩ የአገልግሎት ስፍራዎች አስተዋጽኦ ያደረጋችሁ እንዲሁም ይህንን የደስታ ቀን እንድንመለከት ትብብር ያደረጋችሁ በአብያተ
ክርስቲያናቱ እና በሀገረ ስብከታችን እንዲሁም በሀገራችንና በመላው ዓለም የምትገኙ ምእመናን ሁሉ ትጋታችሁ ውጤት አምጥቷልና እንኳን ለዚህ ቀን አደረሳችሁ እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ፡
የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ሀገራችንን ጽኑ ሰላም ያድርግልን፡፡ ቤተ ርስቲያንንም ይጠብቅልን፡፡ ምእመናንን በፍቅር በአንድነት ያጽናልን፡፡ አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አባ ዮሴፍ
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ
የሲዳማ ክልል የጌዴኦ ዞን የአማሮና ቡርጂ ወረዳዎች
አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ