ነገረ ቁስቋም
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ሰብአ ሰገል በኮከብ ተመርተው በመምጣት ሰገዱለት፤ እጅ መንሻም አቀረቡለት። ሰብአ ሰገልም ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ። ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፥ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ አለው። እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በሌሊት ያዘና ወደ ግብፅ ሄደ፥ ማቴ ፪፥፩-፲፭
እመቤታችን ዮሴፍ እና ሰሎሜ ወደ ምድረ ግብፅ ሲጓዙ ሦስት ቀን ጫካ ውስጥ ሰነበቱ፡፡ በጣም ተራቡ፣ ተጠሙ። በበረሃ በረሃብና በውሃ ጥም እንዳይሞቱ እመቤታችን ጸለየች፡፡ ወዲያው የተሠራ ማዕድ /የተዘጋጀ ምግብ/ መጣላቸው በልተው ጠገቡ፡፡ ከዚህ በኋላ ኢንፍሎን ወደተባለ አገር ሄዱና ርግባዳ ከተባለ ሰው ቤት ተቀመጡ፡፡ ብዙ ሰዎች ዕውቀት ፈልገው ወደ እመቤታችን ይመጡ ነበር፡፡ እመቤታችን ከጥበበኞች ከእስራኤል አገር ስለመጣች ብዙ ጥያቄዎችን ይጠይቋት ነበር፡፡
እመቤታችን ብዙ ምሳሌ እየመሰለች ጥያቄዎቻቸውን ስትመልስላቸው እያደነቁ ይሄዱ ነበር፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የዚያች አገር ገዥ ሞተ፡፡ ቤተሰቦቹ መጥተው ለእመቤታችን ነገሯት፡፡ እመቤታችን ስትሄድ ሞቶ አገኘችው፡፡ የሚያለቅሱትን ሰዎች ዝም በሉ አለቻቸው፡፡ አልቃሾቹ ዝም አሉ፡፡ በቀኝ እጅዋ ይዛ በእግዚአብሔር ስም ተነስ አለችው። የሞተው አገር ገዥ ሕያው ሆኖ ተነሣ፡፡ ለለቅሶ የተሰበሰቡት ሰዎች የጣዖቶቻቸውን ስም በመጥራት አጵሎንና አርዳሚስ ሰው ተመስለው መጡ አሉ።
እመቤታችንም እናንተ የምትሏቸው ጣዖታት አይደለሁም፡፡ ከይሁዳ ምድር ተሰድጄ የመጣሁ ሰው ነኝ ካለቻቸው በኋላ የሞተውን ሰው ማስነሣት የሚቻለው እግዚአብሔር መሆኑን እንዲያውቁና በእግዚአብሔር እንዲያምኑ አስተማረቻቸው፡፡
በሀገራቸው ውስጥ የሚኖሩ በሽተኞችን እየፈወሰችላቸው ጥቂት ወራት ተቀመጠች። ምድራቸውን ባርካ ውሃ አፈለቀችላቸውና በዚህ ተፈወሱ አለቻቸው፡፡ የታመመ ሰውም ሆነ እንስሳ እመቤታችን ባፈለቀችው ውሃ ሲታጠብ ይፈወስ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ራፋን ወደተባለ አገር ሄዱ ፡፡ የራፋን ሰዎች መለከት እየነፉ ወጥተው እመቤታችንን ዮሴፍንና ሰሎሜን በድንጋይ ቀጠቀጧቸው፡፡
እነዮሴፍም ከዚያ አገር ወጥተው ሄዱ፡፡ በአረብ አንፃር ቄድሮስ ከተባለ አገር ደረሱ፡፡ በተቃራኒው የሚጾሙ የሚጸልዩ ደጋግ ሰዎችን አገኙ፡፡ አገሩም በጣም ደስ የሚያሰኝ ልምላሜ የተሞላበት አገር ነበር፡፡ በቄድሮስ ስምንት ወር ተቀመጡ፡፡
ይቀጥላል . . .