ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ ወእግዚእነ በቃለ ቀርን (እግዚአብሔር በእልልታ ጌታችንም በመለከት ድምጽ ዐረገ) መዝሙር 46፤5

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
በቤተክርስቲያናችን ከምናከብራቸው ዓመታዊ በዓላት አንዱ የጌታችን ዕርገት በዓል አንዱ ነው፡፡የጌታችን ዕርገት ከ9ኙ የጌታችን ዐበይት በዓላት አንዱ ነው፡፡ ከትንሳኤ በኋላ በ40ኛው ቀን የሚከበር ነው፡፡ጌታችን እና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃል ለመነገሩ በኅሊና ለመዘከሩ ለስም አጠራሩ ክብር የክብር ክብር ይግባውና፡፡ በነቢያት ያናገረውን ትንቢት በቃሉ የተናገረውን ፈጽሞ ለአዳም እና ለልጆቹ ቤዛ በመስቀል ተሰቅሎ ሞቶ ሞትን እና ሙስና መቃብርን አጥፍቶ በታላቅ ኃይል እና ስልጣን በመነሳት በተለያየ ቀን ለቅዱሳት አንስት እና ቅዱሳን ሐዋርያት በመገለጥ ለ40 ቀናት መጽሐፈ ኪዳንን ካስተማራቸው በኋላ እፍ በማለት ወይም በንፍኃት እና በአንብሮ እድ(እጅን በመጫን) ስልጣነ ክህነትን ሰጣቸው ዮሐ20፤22 ኃይንል ከላይ እስክትቀበሉ ድረስ በኢየሩሳሌም ቆዩ ብሎ በማዘዝ፡፡ የሐዋ 1፤4 ሁሉም እያዩት በመርቀቅ ሳይሆን በመራቅ ወደላይ ዐረገ የሐዋ 1፤9 ይህ በመጽሐፍ የተጻፈ፣ በህይወት የታየ ለአህዛብ የተሰበከ እውነት እና ህይወት ነው፡፡ ከላይ በርእሳችን እንዳነሳነው እግዚአብሔር በእልልታ ጌታችንም በመለከት ድምጽ ዐረገ በማለት የጌታን ዕርገት በትንቢት ተናግሮ ነበር፡፡
የክርስቶስ እርገት የቤተክርስቲያን ድኅነት (ደኅንነት) እና መለኮታዊ ኅብረት ተሳትፎ ሱታፌ አምላክ (ቴዎሲስ/theosis) ጥልቅ የሆነ የነገረ መለኮት እውነት ነው። የሰውን ባሕርይ ለማክበር እና የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ኅብረት ለመመለስ ክርስቶስ ዐርጓል፡፡የክርስቶስ ትንሳኤ እና ዕርገት የሰውን ልጅ ወደቀደመ እርስቱ ከዛም ከፍ ወደሚል ወደ ሱታፌ አምላክ የእግዚአብሔር የመለኮቱ ባህርይ ተካፋይ አድርጎናል፡፡ ምን ማለት ነው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን በባህርይ ለማየት ጨርሶ የማይችል ሲሆን ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር የእኛን ስጋ ተዋህዶ ረቂቁ በመግዘፍ ግዙፉን አረቀቀው፣በዝግ ቤት እንዲገባ አደረገው በሁሉ የሚገኝ አምላክ ውሱን ስጋን ተዋህዶ ለሐዋርያት ታየ፡፡ የማይዳሰስ እሳት የሚዳሰስ ስጋን በመዋሃድ በቶማስ እንዲዳሰስ አደረገው፡፡ ይህንኑ በዝግ ቤት የገባውን በቶማስ የተዳሰሰውን ስጋ ወደ ሰማይ አሳረገው፡፡ ወጣ ወረደ የማይባል በሁሉ ያለ መለኮት ወጣ ወረደ የሚባል ስጋን በመዋሐዱ ዐረገ ለማለት አበቃን፡፡ ምን ያህል እንዳከበረን ተመልከቱ አዳም አምላክነትን ፈልጎ እጸበለስን ቢበላ ውርደት ነበር ያገኘው፡፡ወልደ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ አዳም የተመኘውን አምላክነት አምላክ ሰው ሆኖ ከመለኮቱ ተካፋይ በማድረግ ሰጠው፡፡ ይህ እግዚአብሔር ሰውን ምን ያህል እንዳከበረው የሚያሳይ ሲሆን እኛ እግዚአብሔር ባከበረን ልክ ከብረን ክብራችንን ጠብቀን እንኖራለን ወይ ወይስ እንደ እርያ ታጥበን ጭቃ ላይ እንንከባለላለን እግዚአብሔር ባከበረን ልክ ነን ወይ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይገባናል፡፡ ከወደቅንበት አዘቅት ለማንሳት አምላክ ወደ ምድር ወረደ የወደቅነውን አንስቶ በሰማያዊ ማዕረግ ላይ አስቀመጠን፡፡ በዚህ መጠን ለወደደን አምላክ ክብር ምስጋና ይሁን፡፡
ከበዓለ ዕርገቱ በረከት ረድኤት ይክፈለን፡፡
