ወደ ይርጋለም ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን መጓዣ መንገዶች
ምእመናን ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እና ከውጭ ሀገር እንደሚመጡ ቢታወቅም ከሁሉም መነሻዎች የሚኖሩ የጉዞ አማራጮችን ለማቅረብ አዳጋች ስለሚሆን ከአዲስ አበባ ጀምሮ ያሉ አማራጮች ላይ እናተኩራለን። ከአዲስ አበባ ወደ ይርጋለም ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን ለመምጣት ምእመናን ቢያንስ ከዚህ በታች የተጠቀሱ ሦስት አማራጮች አሏቸው።
1. በአውቶቡስ
ከአዲስ አበባ ወደ ወደ ሀዋሳ የሚጓዙ አብዛኛዎቹ አውቶቡሶች በዋናነት መነሻቸው ላምበረት መናኸሪያ ሲሆን ከቃሊቲ እና መርካቶ መናኸሪያዎች የሚነሱ አውቶቡሶችም አሉ። ጉዞው የሚወስደው ጊዜ እንደመኪናው የሚወሰን ቢሆንም በአማካኝ አምስት ሰዓት ሊወስድ ይችላል።
አብዛኛዎቹ አውቶቡሶች የሀዋሳ መዳረሻቸው አሮጌው መናኸሪያ አካባቢ ስለሆነ ምእመናን ሀዋሳ ከደረሱ በኋላ ወደ ይርጋዓለም የሚጓዙ መኪናዎችን ለማግኘት ወደ አዲሱ መናኸሪያ በታክሲ ወይም በባጃጅ መጓዝ አለባቸው። ወደ ይርጋለም የሚጓዙ መኪናዎችን ከተሳፈሩ በኋላ ይርጋዓለም መናኸሪያ ከመድረሳቸው በፊት ይርጋለም ቅድስት አርሴማ መገንጠያ መውረድ ይኖርባቸዋል። ከአዲሱ መናኸሪያ ጀምሮ መገንጠያው ድረስ በአማካኝ አንድ ሰዓት ሊወስድ ይችላል። ምእመናን ይርጋለም ቅድስት አርሴማ መገንጠያ ከደረሱ በኋላ በእግር፣ በሞተር ወይም በባጃጅ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ መጓዝ ይችላሉ። በእግር ለሚጓዙ በአማካኝ 20 ደቂቃ ሊወስድ ይችላል።
2. በግል መኪና
በግል መኪና ከአዲስ አበባ የሚመጡ ምእመናን የተሻለ አማራጭ የሚሆነው ፈጣን መንገዱን መጠቀም ሲሆን መንገዱ ግልጽ የሆኑ ጠቋሚ ምልክቶች ያሉት በመሆኑ ቀና ነው። በጉዟቸውም ቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት)፣ ባቱ (ዝዋይ)፣ ሻሸመኔ፣ ሀዋሳ እና በመካከል የሚገኙ ሌሎች ከተሞችን ያልፋሉ። እንደ መንገዱ ሁኔታ አንዳንዶቹን ከተሞች ወደ ውስጥ ሳይገቡ በዳር ሊያልፏቸው ይችላሉ። ከአዲስ አበባ እስከ ቤተ ክርስቲያኑ ድረስ በአማካኝ ስድስት ሰዓት ሊወስድ ይችላል። መኪና ይዘው ለሚመጡ ምእመናን በቤተ ክርስቲያኗ ግቢ ውስጥ በቂ የመኪና ማቆሚያ እና ጥበቃ አገልግሎት ይሰጣል።
3. በአውሮፕላን
በአውሮፕላን የሚመጡ ምእመናን ከቦሌ አየር ማረፊያ የሀገር ውስጥ በረራ ጣቢያ እስከ ሀዋሳ አየር ማረፊያ ድረስ በአውሮፕላን መጓዝ የሚችሉ ሲሆን ከዚያ በኋላ ያለውን ጉዞ በመኪና መጓዝ ይኖርባቸዋል። ከቦሌ አየር ማረፊያ ሀዋሳ ለመድረስ በአማካኝ 35 ደቂቃ ይወስዳል። ሀዋሳ አየር ማረፊያ ከደረሱ በኋላ ለመንገደኞች በተዘጋጀ አውቶቡስ እስከ ሀዋሳ ከተማ ሳውዝ ስታር ሆቴል ድረስ መጓዝ ይችላሉ። ሀዋሳ ከደረሱ በኋላ ከላይ በአውቶቡስ ለሚጓዙ ምእመናን የገለጽነውን በመከተል ከሳውዝ ስታር ሆቴል ወደ አዲሱ መናኸሪያ ተጉዘው ከአዲሱ መናኸሪያ ወደ ይርጋለም የሚጓዙ መኪናዎችን መጠቀም ይችላሉ።
