ዝክረ ቅዱሳን

ቅዱስ ያሬድ

ቅዱስ ያሬድ ውልደትና እድገቱ ኢትዮጵያ ወስጥ፤ አክሱም ከተማ ከአባቱ ከአብዩድና ከእናቱ ታውክሊያ ነው፤ ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ እናቱ መምህር ወደ ሆነው አጎቱ አባ ጌዲዬን ትወስደዋለች፡፡ እርሱ ግን በመጀመሪያ ትምህርት ሊገባው አልቻለም፡፡ ከዕለታት በአንድ ቀን መምህር ጌዲዬን ያሬድን ሲገርፈው በምሬት አለቀሰ፤ ማይኪራህ ወደምትባል ቦታም ተጓዝ፤ በመንገድ ላይ ሳለ ውሃ ስለጠማ በዚያች ስፍራ ካለ ምንጭ ውሃ ጠጥቶ በዛፉ ሥር ለማረፍ ቁጭ አለ፤ ወደ ላይም በሚመለከትበት ጊዜ ከዛፉ ላይ አንዲት ትል ከታች ወደ ላይ ስትወጣ ስትወርድ ተመለከተ፡፡ እርሱም ትኩር ብሎ አያት፤ ትሏም ያለመሰልቸት ከወጣች ከወረደች በኋላ ዛፉ ላይ መድረስ ቻለች፡፡

በዚያን ወቅት ቅዱስ ያሬድ አሰበ፤ እንዲህም አለ፤ «ይህች ትል ዛፉ ላይ ለመድረስ እንዲህ ከተጋች እኔም ትምህርት ለመማር ብታጋ እግዚአብሔር አምላክ ይገልጽልኛል»፡፡ ወደ ጉባኤው ተመልሶ መምህሩን ይቅርታ ከጠየቀ በኋላ መማር ጀመረ፤ እግዚአብሔር አምላክም የ፹፤፩ መጽሐፍትንና የሊቃውንት መጽሐፍትን እንዲሁም ሌሎች ቤተ ክርስቲያን የተቀበለቻቸውን የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር ገለጸለት፤ መምህር ጌዲዬን ሲሞት የእርሱን ቦታ ተረክቦ ማሰተማር ቀጠለ፡፡

በ፭፻፴፬ዓ.ም. ኅዳር ፮ ቀን፤ ወደ ሰማይ ተመነጠቀ፤ በሰማይ ቅዱሳን መላእክት እግዚአብሔርን ልዩ በሆነ ጣዕመ ዝማሬ ሲያመሰግኑ ሰማ፡፡ ወደ ምድርም በተመለሰ ጊዜ አክሱም ጽዮን ውስጥ ወደ ምስራቅ በኩል በመዞር ከሰማይ የሰማውን ዝማሬ ዘመረ፤ አርያም ብሎም ሰየመው፡፡ በዚሁም በ፭፻፴፰ ዓ.ም. ቅዱስ ያሬድ ማኅሌትን ጀመረ፡፡

ይቀጥላል . . .