ገድለ ቅድስት አርሴማ
ቅዱሳን፣ ጻድቃን እና ሰማዕታት የልዑል እግዚአብሔርን ትዕዛዝ ከማክበር ባለፈ እርሱን ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ ተጋድሎን በማድረግ ለብዙዎች ፋና የሆኑ ናቸው። ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም እኛ ልጆቿ እንማርበት፣ እንባረክበት እና ለጸሎት እንጠቀምበት ዘንድ የተጋድሏቸውን ዜና እና ያደረጓቸውን ተኣምራት በመጻፍ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ታደርጋለች።
ሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ ጌታችን በወንጌሉ “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” (ማቴ። ፲፮፥፳፬) ያለውን ተግባራዊ ያደገች ገድለኛ ሰማዕት ስትሆን የቀደሙ አባቶቻችን ገድሏን በመጻፍ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ አድርገውልናል። ሆኖም “የሰማዕቷ የቅድስት አርሴማ ገድል” ነው በማለት ዕውነተኛነት የሚጎድላቸው እና ሕጸጽ የበዛባቸው በዓይነትም በይዘትም የተለያዩ መጻሕፍት በገበያ ውስጥ በብዛት ሲሰራጩ ኖረዋል። እነዚህ መጻሕፍት ከትክክለኛው ምንጭ ያልተቀዱ እና ገንዘብ ማግኘትን አላማ ያደረጉ እንዲሁም የሰማዕቷ የቅድስት አርሴማን ተጋድሎ በትክክል የማይገልጹ በመሆናቸው ሰማዕቷ ያዘነችባቸው ናቸው።
ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ የሚሰራው ልዑል እግዚአብሔር የፈቀደው ጊዜ ደርሶ በእርሱ ቸርነት በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እና በሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ ተራዳኢነት በግዕዝ የተጻፈውን ጥንታዊውን የብራና ገድል ወደ አማርኛ በመመለስ (በመተርጎም) በይርጋ ዓለም ደብረ ታቦር ቅድስት አርሴማ እና ደብረ ቁስቋም ቅድስት ማርያም አብያተ ክርስቲያናት እንዲታተም ለማድረግ ተችሏል። ይኽንን ላደረገልን ለአምላከ ቅድስት አርሴማ ለልዑል እግዚአብሔር ክብርና ምስጋና ይግባው።
ገድለ ቅድስት አርሴማ መጽሐፍ የቅድስት አርሴማን ገድል፣ ተኣምር እንዲሁም መልክእ አጠቃሎ የያዘ ሲሆን በግዕዝና በአማርኛ የተዘጋጀ መጽሐፍ ነው። የቅድስት አርሴማ ገድል አሥራ ስምንት ምዕራፎችን የያዘ ሲሆን ለሰባቱ ቀናት የተከፋፈለ ነው።
ከገድሏ በመቀጠል ሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ ያደረገችው ተኣምር በመጽሐፉ የቀረበ ሲሆን ተኣምራቱ ገድለኛዋ እና ሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ በተጋድሎዋ ወቅት እና በዚህ ዘመን ያደረገቻቸውን ተኣምራት ያካተተ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ “ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል” (ዮሐ ፳፩፥፳፭) እንዳለ ሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ ያደረገቻቸው ብዙ ተኣምራት ቢኖሩም ሁሉንም በዚህ መጽሐፍ ማካታት እንደማይቻል ልንገነዘብ ይገባል። የሰማዕቷን ድንቅ ተኣምራት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ወደፊት በህትመት፣ በድረ ገጽ እና በሌሎች መንገዶች ለምዕመናን እንዲደርስ የምናደርግ ይሆናል።
የቅድስት አርሴማ ገድል ሦስተኛው ክፍል መልክአ ቅድስት አርሴማን የያዘ ሲሆን ከአሁን በፊት በግዕዝ ታትሞ ምዕመናን ለጸሎት ሲጠቀሙበት የነበረውን በማረም እና ወደ አማርኛ በመመለስ የተዘጋጀ ነው።
ሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ በጸሎቷ “መታሰቢያችንን የሚያደርገዉን፣ የተጋድሏችንንም መጽሐፍ የሚያጽፈዉን፤ በጸሎታችንም (በምልጃችንም) የታመነዉን፣ አንተ ይቅር በለው፤ በንጹሕ ፍቅርኽም ጤናን ስጠው። አቤቱ በእውነት የለመነኽን በኾነው ነገር ኹሉ ረዳትን ኹነው።” ብላ ልዑል እግዚአብሔርን በለመነችው ጊዜ “ምኞትሽ ኹሉ እንደ ቃልሽ ይደረግልሽ” (ገድለ ቅድስት አርሴማ ፲፰፥፶፰-፷) ብሎ የሰጣትን ቃል ኪዳን በማመን ምዕመናን ይኸነን ገድለ ቅድስት አርሴማ በሚገባ አክብረው በመጠቀም እና በጸሎቷ በመታመን ከሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ እንዲያገኙ እንጋብዛለን።