ተኣምር
ስሜ መና ሲሆን የመጣሁት ከድሬዳዋ ነው። የዲስክ መንሸራተት ሕመም ያሰቃየኝ ስለነበር ለአሥር ደቂቃ ያህል እንኳን መቀመጥ አልችልም ነበር፤ በመኪናም መሄድ አልችልም ነበር። ሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ ወዳጅዋን ልካልኝ “ለምን ይርጋለም ቅድስት አርሴማ አትሄጂም?” አለኝ። እኔም ወደዚህ ቦታ መጥቼ ለሦስት ቀን ሱባኤ ገባሁ ከሱባኤው በፊት ራሴን ችዬ ሳልደገፍ መቀመጥ አልችልም ነበር። ሱባኤ ቤት ውስጥ ግን መሐል ላይ ያለ ግድግዳና ትራስ ድጋፍ መቀመጥ ቻልኩ፤ መቆምም ይከብደኝ ነበር ሱባኤ ቤት ውስጥ ሆኜ ሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ መቆም አስችላኛለች። ከሱባኤውም በኋላ ጤናዬን አግኝቻለሁ፤ ሰማዕቷም ከእኔ ጋር ናት፤ አልተለየችኝም። እኔም አመሰግናታለሁ። እኔን እንደሰማች ሁሉንም ትስማ፡፡
ስሜ ዘነበች ወርቁ (እህተ ማርያም) ሲሆን የመጣሁት ከአሜሪካ አትላንታ ነው። ሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ ያደረገችልኝ ድንቅ ተኣምር ይኽ ነው። ሙሉ ውስጤን ይህ ነው የማልለው ሕማም ነበረብኝ፤ ያለሁበት ሀገር ውስጥ የሚገኙ ብዙ ዶክተሮች አይተውኝ ምንም ሊረዱኝ አልቻሉም። ከቀን ወደ ቀን እየባሰብኝ መጣ፤ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ወደሚገኙ ቤተሰቦቼ ስልክ ደወልኩና ሕማሜን ነገርኳቸው፤ በቤተ ክርስቲያንም ጸሎት እንዲደረግልኝ ያደርጉ ዘንድ አሳሰብኳቸው። የቤተሰቦቼ ጎረቤት የሆነች አንዲት ልጅ ይህን ስትሰማ ከይርጋለም ቅድስት አርሴማ ያመጣችውን ማርና ሽንብራ ላከችልኝ። እኔም በሙሉ እምነት ሰማዕቷ ቅድስት አርሴማን እየተማፀንኩ ማሯን እና ሽንብራዋን በአግባቡ ተጠቀምኩት። እናቴም አላሳፈረችኝም በማሯና በሸንብራዋ ፈውሳኛለች። በተጨማሪም መልካም ትዳርና ልጅ ሰጠችኝ በሰላምና በጤና እየኖርኩ ነው ለእኔ ፈጥና የደረሰች እናት ለሁላችሁም ትድረስ፤ ሰማዕቷን አመስግኑልኝ፡፡
ስሜ ዘነበ ሲሆን የመጣሁት ከዳውሮ ዞን ነው። ለሠላሳ ዓመት ያህል በሱስ ተጠምጄ ስሰቃይ ነበር፤ ወደ ሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን መጥቼ ሱባኤ ገባሁ። ሰማዕቷንም ካለብኝ ሱስ እንድታላቅቀኝ ለመንኳት። ርሷም ልመናዬን ሰምታ የነበረብኝ ሱስ አስወግዳ ፍፁም ጤናዬን ሰጥታኛለች፡፡
ስሜ ከበቡሽ ይልማ ሲሆን ሰማዕቷ ያደረገችልኝ ድንቅ ተኣምር ይኽ ነው። በእግሬ መሄድ ስለማልችል በዊልቸር ነበር የምሄደው። በነበረብኝ ሕማም የተነሳ ብዙ ስሰቃይ ነበር፤ መንቀሳቀስም ሆነ ሽንት ቤት መቀመጥ አልችልም ነበር። የሰማዕቷ ቅድስት አርሴማን ፈዋሽነት በማመን ወደ ቤቷ መጥቼ ለሰባት ቀን ሱባኤ ገባሁ፤ ሰማዕቷም ፈወሰችኝ። ከዚያ በኋላ በእግሬ መሄድ ጀምሬያለው። ይህን ድንቅ ተኣምር ስላደረገችልኝ እና ከፈጣሪዋ አማልዳ ስላስማረችኝ ሰማዕቷን አመስግኑልኝ፤ እኔን የሰማች እናንተንም ትስማ፡፡
ገድለኛዋ እና ሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ ካደረገችው ብዙ ተኣምራት ጥቂቱን ከዚህ በታች አቅርበንልዎታል። ተጨማሪ ተኣምራትን ከገድሏ መጽሐፍ ላይ ማግኘት ይችላሉ።