በይርጋ ዓለም ደብረ ታቦር ቅድስት አርሴማ እና ደብረ ቁስቋም ቅድስት ማርያም አብያተ ክርስቲያናት የሚሰጡ አገልግሎቶች

የይርጋ ዓለም ደብረ ታቦር ቅድስት አርሴማ እና ደብረ ቁስቋም ቅድስት ማርያም አብያተ ክርስቲያናት የቤተ መቅደስ እና ሌሎች አገልግሎቶች በተሟላ ሁኔታ የሚከናወኑ ሲሆን ለየት የሚሉትን
እንደሚከተለው አቅርበንልዎታል።

  1. ሱባኤ፡ ሱባኤ የሚገቡበት እና አርምሞ በመያዝ ለጸሎት የሚተጉበት የሱባኤ ቦታ የተዘጋጀልዎት ሲሆን ከእርስዎ የሚጠበቀው የሱባኤውን ሥርዓት በጥንቃቄ መጠበቅ እና በጸሎት መትጋት ነው። በሱባኤ ወቅት ተግባራዊ ማድረግ ስላለብዎት ሥርዓት በዝርዝር የሚያስረዳ መመሪያ በአግባቡ መማር እና በጥንቃቄ መተግበር ይኖርብዎታል። በሱባኤ ቤት መቆየት የሚችሉት ከፍተኛ ጊዜ ሰባት ቀን ሲሆን ከዚያ በታች ግን እርስዎ ባቀዱት ቀን መውጣት ይችላሉ።
  2. ጸበል፡ በሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ ፈዋሽ ጸበል ለመጠመቅ (ለመጸበል) ሲመጡ በቅድሚያ ተመዝግበው ማረፊያ ቦታ ይሰጥዎታል። ተግባራዊ ማድረግ ስላለብዎት ሥርዓት በዝርዝር የሚያስረዳ መመሪያ ስለሚሰጥ እርሱን በአግባቡ መማር እና በጥንቃቄ መተግበር ይኖርብዎታል። ስለ ግቢዋ ሥርዓት ቤተ ክርስቲያኗ ከምታስተምረው ውጭ የሆነ ነገር ሌሎች ሰዎች ቢነግሩዎትም መቀበል የለብዎትም። በቆይታ ጊዜ በሚሰጥዎት ማረፊያ በመጽናት እና አርምሞ በመያዝ ጸበል መጠመቅ ይኖርብዎታል።ለጸበል መቆየት የሚችሉት ከፍተኛ ጊዜ ሰባት ቀን ሲሆን ከዚያ በታች ግን እርስዎ ባቀዱት ቀን መውጣት ይችላሉ።
  3. የሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ ፈዋሽ ጸበል ማንኛውንም በሽታ የሚፈውስ ሲሆን ከጸበሉ ጎን ለጎን መድኃኒት መጠቀም ላለባቸው እንዲሁም የማይቋረጥ መድኃኒት ለሚጠቀሙ እንደ ስኳር፤ኤችኢይቪ እና መሰል ሕመምተኞች የተለየ ማረፊያ ቦታ የተዘጋጀ ሲሆን ከጸበል በኋላ መድኃኒታቸውን መጠቀም የሚችሉበት ሁኔታ ተመቻችቶላቸዋል። በተጨማሪም ለሕጻናት እና ለአእምሮ ሕሙማን የተለየ ቦታ ተዘጋጅቶላቸዋል።
  4. የሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ ጸበልም ሆነ እምነት (የግቢዋ አፈር) ከግቢዋ የማይወጣ እንደመሆኑ በሰማዕቷ የተፈቀደ እና የተባረከ ፈዋሽ ማር እና ብርዝ ገዝተው መጠቀምም ሆነ ወደ ቤት ይዘው መሄድ ይችላሉ። ፈዋሽ ማሯን እና ብርዟን ሲጠቀሙ የአጠቃቀም ሥርዓቱን በሚገባ ማወቅ እና መተግበር ይኖርብዎታል።
  5. ለሱባኤም ሆነ ለጸበል ሲመጡ በቆይታዎ የሚያስፈልግዎትን በሶ፤ ሽንብራ እና የተሟላ የመገልገያ ዕቃዎች እንዲሁም ነጠላ እና ሌሎች ቀለል ያሉ አልባሳትን በግቢዋ ከሚገኘው የሽያጭ ማዕከል ማግኘት ይችላሉ።
  6. የተለያዩ የጸሎት መጻሕፍት፤ ገድላት እና ድርሳናት እንዲሁም በሃይማኖት የሚያንጹ ሌሎች መንፈሳዊ መጻሕፍትን በግቢዋ ከሚገኘው የሽያጭ ማዕከል ማግኘት ይችላሉ።

በይርጋ ዓለም ደብረ ታቦር ቅድስት አርሴማ እና ደብረ ቁስቋም ቅድስት ማርያም አብያተ ክርስቲያናት የሚሰጡ አገልግሎቶች ከላይ የተጠቀሱትን እና ሌሎችን የቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶች በተሟላ ሁኔታ ማግኘት የሚችሉ ሲሆን ከእርስዎ የሚጠበቀው የግቢዋን ሥርዓት መጠበቅ እና በጸሎት መትጋት ነው። ወደ እዚህ ቅዱስ ቦታ መጥተው የሚማጸኑ በሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ ቃል ኪዳን በነፍስም በሥጋም የሚጠቀሙ እና የልቦናቸው በጎ መሻት የሚፈጸምላቸው ስለሆነ እርስዎም የበረከቱ ተካፋይ እንዲሆኑ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡