“በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ።” (ሮሜ 12፥12)
“በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ።” (ሮሜ 12፥12)
ሰላም ለእናንተ ይሁን የቅድስት አርሴማ ወዳጆች በዛሬዉ የትምህርት አምዳችን ስለ ተስፋ ኃይል ልናጋራቹ ወደድን። ተስፋ ማለት ገና ያልሆነውን ነገር ሆኖ እንደማየትና በዚያ መታመን ነው። ለዚህ ደግሞ ትልቁ አርአያችን አባት አብርሃም ነው።
አብርሃም ልጅ ያገኛል ተብሎ ተስፋ በማይደረግበት እድሜ ላይ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “ዘርህ እንዲሁ ሊሆን ነው እንደ ተባለ፥ ተስፋ ባልሆነው ጊዜ የብዙ አሕዛብ አባት እንዲሆን ተስፋ ይዞ አመነ።” ይለናል (ሮሜ 4፥18)። አብርሃም የተመለከተው የራሱን ድካም ወይም የሣራን መካንነት ሳይሆን፣ ተስፋ የሰጠውን አምላክ ታማኝነት ነበር። ለዚህም ነው ከቤቱ ወጥቶ ባልታወቀ ምድር ሲጓዝ፣ ቃሉ ገና ሳይፈጸም በደስታና በሰላም መኖር የቻለው።
ተስፋ በሁኔታዎች አይወሰንም፦ ነገሮች ዛሬ ቢጨልሙም፣ አብርሃም እንዳደረገው ዓይናችንን በተስፋው ባለቤት ላይ ካደረግን ውስጣዊ ደስታችን አይጠፋም።
መጠበቅን በደስታ ማሳለፍ፦ አብርሃም ተስፋው እስኪፈጸም ብዙ ዓመታትን በትዕግሥት ጠብቋል። እኛም በሕይወታችን፣ በሥራችንም ሆነ በቤታችን የምንጠብቀው ነገር ሲዘገይ ልባችን ሊዝል አይገባም።
ውድ ቤተሰቦቻችን፣ ዛሬ በሥራ ውጥረትም ሆነ በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ ብትሆኑም፣ እንደ አብርሃም በተስፋ ጽኑ። ተስፋ ካለን ደስታችን አይነጠቅም፤ ምክንያቱም ተስፋ የምናደርገው አምላክ ታማኝ ነው።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
